Thursday, July 3, 2014

የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ሥራ አስፈፃሚ መንግስት በአዲስ አበባ የፓርቲው አባላት ላይ የሚፈጽመውን ውንብድና በመቃወም መግለጫ አወጣ

 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
 
Finote nestanet added 2 new photos.
የአንድነት ፓርቲ የአዲስ አበባ ሥራ አስፈፃሚ መንግስት በአዲስ አበባ የፓርቲው አባላት ላይ የሚፈጽመውን ውንብድና በመቃወም መግለጫ አወጣ
*************************************************
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
***********************************************
መንግሥታዊ የውንብድና ጥቃት በአስቸኳይ ይቁም !!
**********************************************
ከአዲስ አበባ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ
**************************************
የሕወሓት /ኢህአዴግ ቡድን ለአለፉት 23 ዓመታት ወደር የሌለው የሰብአዊ መብት ረገጣ በዜጎች ላይ ሲፈጽም መቆየቱ ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ይህ የሰብአዊ መብት ረገጣ በእጅጉ ተባብሶ ወደ መንግሥታዊ የውንብድና ጥቃት ተቀይሯል፡፡ ዜጎች መንግሥት ባሰማራቸው የደህንነት ኃይሎች ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ በጅምላ ይታሰራሉ፣ ይደበደባሉ፣ በስውር እስርቤቶች ተወርውረው ደብዛቸው እንዲጠፋ ይደረጋል፡፡
መንግሥት በየጊዜው የሚያወጣው የሀሰት፣ አድገናል፣ ተመንድገናል፣ ዜጎች ዕልል በሉ በማለት የሚያናፍሰው ባዶ ፕሮፓጋንዳ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሲያጣ ወደ ተቃዋሚ ኃይሎች ጣቱን በመቀሰር የተደራጀ የማፍያ ቡድን በግልጽ በማሰማራት በጠራራ ፀሐይ የውንብድና ተግባር በማስፈፀም ላይ ይገኛል፡፡
‹‹መንግሥት ሀገር ማስተዳደር እንዳልቻለ አዲስ አበባ ማሳያ ነች!›› በማለት የአዲስ አበባ አንድነት ም/ቤት ባዘጋጀው ሰላማዊ ሠልፍ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው የተሳተፉበት የእሪታ ቀን በተሳካ ሁኔታ ከተጠናቀቀ ጊዜ ጀምሮ በአንድነት ፓርቲ አመራርና አባላት ላይ የሚፈጽመው አሳፋሪ መንግሥታዊ ጥቃት ኢህአዴግን ወደ ተራ ውንብድና መውረዱን የሚያሳየን ሃቅ ነው፡፡
ባለፉት 2 ወራቶች በአዲስ አበባ የአንድነት አባላቶች ላይ ከትንኮሳ ጀምሮ እስከ አካል ማጉደል ወንጀል ኢህአዴግ ባደራጃቸው የደህንነት መታወቂያ በያዙ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሞብናል፡፡
እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በጠራራ ፀሐይ የሰው ጥርስ አውልቀው፣ ጭንቅላት ፈንክተው በተዘጋጀላቸው መኪና ተኩራርተው በአደባባይ ሲሄዱ አንድም የፀጥታ ኃይል ሊያስቆማቸው ያለመቻሉ ኢህአዴግ መንግሥታዊ የውንብድና ጥቃት በአንድነት ፓርቲ ላይ እየፈፀመ ለመሆኑ በቂ ማረጋገጫ ነው፡፡

የእዚህ መንግሥታዊ የውብድና ጥቃት ሠለባ የሆኑት አባሎቻችን ፡-
1ኛ አቶ ስንታየሁ ቸኮል የአዲስ አበባ አንድነት ሥራ አስፈፃሚና የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ
ግንቦት 12 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በቀን በውንብድና ተግባር ተደብድቦ ጭንቅላቱ ተፈንክቷል፡፡
2ኛ አቶ አስራት አብርሃ የብሔራዊ ም/ቤት አባል በስውር እስር ቤት ለቀናት ታስረው በፍርድ ቤት በዋስ ተለቋል፡፡
3ኛ አቶ ፀጋዬ አላምረው የብሔራዊ ም/ቤ አባልና የፓርቲው የሂሳብ ክፍል ኃላፊ በቅድመ ውህደት የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ሰኔ 1ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በኢህአዴግ አባላት ተደብድቧል፡፡
4ኛ ወጣት ጥላዬ ታረቀኝ የአዲስ አበባ አንድነት የም/ቤት አባልና የወረዳ 17 የአንድነት ሥራ አስፈፃሚ በደህንነት ኃይሎች ሰኔ 12 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በቀን ተደብድቧል፡፡
5ኛ አቶ ምሥራቅ ቦጋለ የአንድነት ፓርቲ አባል በወሮበሎች ተደብድቦ ሁለት የፊት ጥርሶቹ ወልቋል፡፡
6ኛ አቶ ደረጀ ጣሰው የአዲስ አበባ ህዝባዊ ንቅናቄ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፓርቲው ለቅስቀሳ አዋሳ በላካቸው ወቅት ከሰኔ 13 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም እስከ ሰኔ 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ድረስ በግፍ በአዋሳ ታስረው በዋስ ተለቀዋል፡፡
7ኛ አቶ ኃይሉ ግዛው የአዲስ አበባ ህዝባዊ ንቅናቄ አብይ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ም/ቤት አባል ፓርቲው ለቅስቀሳ አዋሳ በላካቸው ወቅት ከሰኔ 13 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም እስከ ሰኔ 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ድረስ በግፍ በአዋሳ ታስረው በዋስ ተለቀዋል፡፡
8ኛ አቶ አብርሃም አራጌ የአዲስ አበባ ህዝባዊ ንቅናቄ አብይ ኮሚቴ አባል ፓርቲው ለቅስቀሳ አዋሳ በላካቸው ወቅት ከነመኪናቸው ከሰኔ 13 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም እስከ ሰኔ 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ድረስ በግፍ በአዋሳ ታስረው በዋስ ተለቀዋል፡፡
9ኛ ወጣት መልካሙ አምባቸው በዩኒቨርሲቲ የፓርቲው አደረጃጀት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከግንቦት 18 እስከ ሰኔ 6 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በግፍ ማዕከላዊ ታስሮ በዋስ ተለቋል፡፡
1ዐኛ አቶ እንግዳወርቅ ማሞ የአዲስ አበባ የአንድነት ሥራ አስፈፃሚና ፀሐፊ ሰኔ 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም መንገድ ላይ ጠብቀው በመኪና ለመግጨት ሞክረው ባለመቻላቸው አራት የታጠቁ የደህንነት መታወቂያ የያዙ ኃይሎች በጠራራ ፀሐይ አፍነው ወደ መኪናቸው ለማስገባት ያደረጉት ጥረት በግለሰቡ አልሞት ባይ ተጋዳይነት ቢከሽፍም የጥፋት ኃይሎቹ በያዙት የሽጉጥ ሰደፍ ተደብድበው ሁለት የፊት ጥርሳቸውን አውልቀው አስፓልት ላይ ዘርረዋቸው መኪናቸውን አስነስተው ሲሄዱ አንድም የፖሊስ ኃይል ሊያስቆማቸው አልቻለም፡፡
11ኛ አቶ ሰይፉ ገላጋይ የወረዳ 17 የአንድነት አባል ግንቦት 26 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም በወንጀለኞቹ ተደብድቧል፡፡
12ኛ መ/ር አጥናፉ ሙላቱ ወረዳ 12/13 የአንድነት አባል በፈጠራ ክስ ተመስርቶበት በመንገላታት ላይ ይገኛል፡፡
13ኛ አቶ ሠለሞን ስዩም ወረዳ 12/13 የአንድነት ብ/ሥ/ኮሚቴ የፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ ስውር ጥቃት ተፈጽሞበታል፡፡
ይህ ሁሉ የውንብድና ተግባር በአለፉት ሁለት ወራቶች መንግሥት ባደራጃቸው ወንበዴዎች የተፈፀመ እኩይ ተግባር ነው፡፡ ጥቃቱ ከ2ዐዐ7 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ በፊት የአንድነት ፓርቲን መዋቅር ለማፈራረስ ሆን ተብሎ በህወሓት/ኢህአዴግ የደህንነት ኃይሎች ታቅዶ የሚከናወን ስለመሆኑ ቅንጣት ያህል አንጠራጠርም፡፡ ጥቃቱ ቀጣይነት ያለው እንደሆነ አንዳንድ ፍንጮች ከወዲሁ እያመላከቱን ናቸው፡፡
የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት የአንድነትን አባላትን በማሰቃየትና በማሸማቀቅ፣ በመደብደብ የአካል ማጉደል ጉዳት በማድረስ አባላትን በማዋከብ የሚያደርገውን አስነዋሪ ተግባር እያወገዝን ከእኩይ ተግባራቸውም እንዲታቀቡ እንጠይቃለን፡፡
ኢህአዴግ እየፈፀመ ያለውን መንግሥታዊ የውንብድና ተግባር በአስቸኳይ እንዲያቆም እንዲሁም እስካሁን በተደራጀ መልኩ ወንጀሉን የፈፀሙትን በጉያው ያቀፋቸውን የጥፋት ኃይሎች ቡድን ለህግ እንዲያቀርብ የአዲስ አበባ አንድነት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
ትግሉ ለህገ-መንግሥትና ለሕግ ከማይገዛ አምባገነናዊ አገዛዝ ጋር መሆኑን ጠንቅቀን የምናውቅ በመሆኑ አሁንም ሳንገል እየሞትን ለዴሞክራሲና ለሕግ የበላይነት እውን መሆን ዛሬም ነገም አጥብቀን በሠላማዊ መንገድ ብቻ በመታገል ከሕዝባችን ጋር ለድል እንበቃለን፡፡
ቃል ኪዳናችንን ጠብቀን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት እስኪሆን በጽናት እንቆማለን!!
የአዲስ አበባ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሰኔ 26 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment