Wednesday, July 2, 2014

#‎EthioMuslims‬ ‪#‎EndureTheStrugle‬ via # አብቢን የሁለት አለም ሰዎች የሚገናኙበት ታሪካዊ ቀጠሮ - ቃሊቲ ፍርድ ቤት! ማክሰኞ ሰኔ 24/2006

#‎EthioMuslims‬ ‪#‎EndureTheStrugle‬  via #

አብቢን

የሁለት አለም ሰዎች የሚገናኙበት ታሪካዊ ቀጠሮ - ቃሊቲ ፍርድ ቤት!
ማክሰኞ ሰኔ 24/2006
ሰላማዊ የመብት ትግላችን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን የሁለት ዓለም ሰው አድርጎናል፡፡ ሺዎች በመላው ሃገሪቱ ስለሰብአዊ እና ሃይማኖታዊ መብታቸው ሲሉ ይኖሩበት ከነበረው ቀዬ እና ዓለም ተነጥለው በእውን ከሚታይ እና ከሚዳሰስ ፍርግርግ ጀርባ ተወስነዋል፡፡ እኛ ደግሞ የነፃነት አየር ርቆን ዛሬም ስለመብታችን እየታገልን ከማይታይና ከማይዳሰስ፣ ግን ደግሞ በተግባር ከሚገኝ ፍርግርግ ጀርባ እንገኛለን፡፡ ዓላማ፣ ፅናት እና የነፃነት እጦት አንድ ቢያደርገንም በውጫዊ ህይወታችን ግን የሁለት ዓለም ሰው ከመሆን አላለፍንም፡፡ በዚህ መልኩ እነሆ ሶስተኛ ረመዳናችንን ተቀበልን፡፡
ወኪሎቻችንና በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በእስር የሚሰቃዩ የትግል አጋሮቻችን ያለፉትን ሁለት ረመዳኖች፣ በተለይም የመጀመሪያውን ረመዳን ብርሃን እና ሰው እየናፈቁ በጨለማ ክፍሎች ታጥረው ያለስሁር እና አፍጥር ቀን ከሌት ይፆሙ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ውስጣችን እልህ እና ወኔ የተሞላ ቢሆንም አካላዊ ፍላጎቶቻችንን እያሟላን፣ ከእነሱ በተቃራኒ ሌላ ዓለም ውስጥ ነበርን፡፡ የዘንድሮው ረመዳን ይሄንኑ ዑደት ዳግም ሊያስቀጥል በእጃችን ላይ ይገኛል፡፡
ወኪሎቻችን ያሉበት የቂሊንጦ አስጨናቂ ህይወት እና እለታዊ ፍርድ ቤት የመመላለስ ድካም ሳይበግራቸው ‹‹እንኳን ለረመዳን አደረሳችሁ!›› ሲሉን ማንም አልቀደማቸውም፡፡ ምንም አይነት ህጋዊ ውክልና የሌላቸውና በአምናው ዒድ ቀብሩ በተፈፀመው የቀበሌ ሹመት የመጡ የመጅሊስ ሹመኞች ስልጣናቸው የሚዲያ መስኮት ቢያስገኝላቸውም የህዝብን ጆሮና ልብ ግን እንደተነፈጉ ሰው አልባ ህይወት ይመራሉ፡፡ ሰሚ አልባ ጩኸትም ይጣራሉ፡፡ በተቃራኒው ወኪሎቻችን ከቂሊንጦ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አጃቢ ሳይሻ ሚሊዮኖች በጉጉት የጠበቅነው፣ ደስም የተሰኘንበት ልዩ የረመዳን ዋዜማ መልካም ዜና ነበር - ከዚያኛው ዓለም የመጣው የ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› መልእክት!
ነገ ተራው የእኛ ነው - የዚህኛው ዓለም ሰዎች! ወኪሎቻችን በሚታደሙበት የፍርድ ሂደት ላይ ወንድ እና ሴት ሳንል፣ ልጅ እና አዋቂ ሳንለይ በመገኘት ‹‹ውድ ኮሚቴዎቻችን እንኳን ለረመዳን አደረሳችሁ!›› እንላቸዋለን፡፡ በዚህም የሁለት ዓለም ሰዎች የሚገናኙበት ታሪካዊ ቀጠሮ ይሆናል፡፡ እስር እና እንግልት አካላዊ መለያየት ያደርስ ይሆናል እንጂ መንፈሳችንን ለያይቶ አሳሪዎቻችን የሚናፍቁትን መነጣጠል፣ መረሳሳት፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ህይወት መራቆት እንደማያመጣ በተግባር እናሳያለን፡፡ ነገ የሁላችንም የጠዋት ቀጠሮ የወኪሎቻችንን ፍርድ ቤት መታደም ነው! (በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች እና በክልል ታሳሪ የሆኑ ጀግኖቻችንን ቤተሰቦች አስመልክቶ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች በቀጣዮቹ የረመዳን ሳምንታት ውስጥ በአላህ ፈቃድ የሚኖሩን ይሆናል!)
የነገ ቀጠሯችንን በቃሊቲ ፍርድ ቤት በማድረግ ለጀግኖቻችን የ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› መልእክታችንን እናድርስ!
ትግሉ የጽኑዎች ነው!
ድምፃችን ይሰማ!

No comments:

Post a Comment