Thursday, July 3, 2014

... "ተነጣጥላችሁ ተቃወሙኝ" Vs. "መስሚያችን ጥጥ ነው"...Dagu Ethiopia via አብቢን

 
........... "ተነጣጥላችሁ ተቃወሙኝ" Vs. "መስሚያችን ጥጥ ነው".............
ሰሞኑን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በየመን መታገት አስመልክቶ በብዙሐን ኢትዮጵያውያን እየተስተጋባ የሚገኘውን "አንዳርጋቸው ይፈታ" ተቃውሞ በግለሰቡና በፓርቲቸው የተመረጠውን የትግል ስልት ከመደገፍ ጋር ለማያያዝ እየተሞከረ ነው፡፡ Daniel Berhane የተባለ የስርአቱ ደጋፊ በፌስ ቡክ ገፁ "የጦርነት አማራጭ አስፈላጊ/ተገቢ አይደለም ካልክ - … ለሱ ጥብቅና መቆም አትችልም፡፡ አንዳርጋቸው … ‹‹ምንም አላጠፋም›› ለማለት ከፈለግህ - ልክ እንደ ብርሀኑ ነጋ፤ <<በኢትዮጲያ ያለው መንግሰት ፋሺስታዊ ነው>> የሚል ግልጽ አቋም መያዝ ይኖርብሀል" በማለት የአንዳርጋቸውን መፈታት መጠየቅን "የጦርነት አማራጭ አስፈላጊ ነው" ከማለት ጋር ለማያያዝ ሞክሯል፡፡
ይህ የስርአቱ ስልት ውስጣዊ ሴራ ግልጽ ነው - የአንዳርጋቸው ይፈታ ጥያቄን ከመላ የዲሞክራሲ ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያን ጥያቄነት በማንኛውም አማራጭ ስርዓቱን በማውረድ አስፈላጊነት ወደሚያምኑ ብቻ ጥያቄነት ማውረድ፡፡ በሌላ አነጋገር በሐገራችን ለውጥ መምጣት ያለበት በሠላማዊ ትግል ብቻ ነው ብለው የሚያምኑ ሐይሎች ለጥያቄው የሚሰጡትን ድጋፍ ስልታዊ በሆነ መንገድ ለማስቀረት የተደረገ ጥረት ነው፡፡ እውነታው ግን የትግል ስልት ልዩነት የስትራቴጂ ልዩነት እንዲ የግብ ልዩነት አለመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ለውጥን በሰላማዊ መንገድ ለማምጣት የሚታገሉ ኃይሎችም ሆነ ሁለገብ ትግል (ነፍጥንም ጨምሮ) በማካሔድ ለውጥ እናመጣለን የሚሉ ወገኖች በርካታ የሚያስማሟቸው ነጥቦች አሉ፡፡ "በኢትዮጵያ ውስጥ አምባገነንነትና ጭቆና አለ" - ሁለቱንም ወገኖች ያስማማል፡፡ "ይህ አምባገነንነትና የመብት ረገጣ በጊዜ መፍትሔ ካልተገኘለት እንደሐገር የመቀጠላችን ዕድል አደጋ ላይ እየወደቀ ይሄዳል" - አሁንም ሁለቱንም ያስማማል፡፡"ለዚህ ችግር መፍትሔ አሁን ያለውን ስርአት አውርዶ በነፃ ምርጫ ህዝቦች የሚፈልጉትን መንግስት እንዲሾሙ ማድረግ ነው" - ልዩነት የለም፡፡ ይህን እንዴት እውን እናደርጋለን? የሚለውን በተመለከተ በእርግጥም ልዩነቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ልዩነቶች ያሉት በሰላማዊ ትግል እና በሁለገብ ትግል አራማጆች መካከል ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ ትግል አራማጆቹ በራሳቸውም ውስጥ ጭምር ነው፡፡ አንዳንዶቹ በምርጫ አሸንፈው ስርአቱን ለመቀየር ሲፈልጉ ሌሎቹ ደግሞ በህዝባዊ እምቢተኝነት ስርአቱን በማስገደድ ወደ ብሔራዊ እርቅ መሸጋገርን ይመርጣሉ፡፡
ነገር ግን የስልት ልዩነቶች በአንድ ፓርቲ መካከል እንኳን የሚከሰቱና ጤነኛ ልዩነቶች ናቸው፡፡ መፍትሔውም በውይይት ልዩነቶችን ማጥበብ፣ ይህ ካልሆነም ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በመከባበር በሚያስማሙ ነጥቦች ላይ በጋራ መስራት ነው፡፡
በዚህ መርህ መሠረት በሁለገብ ትግል አቀንቃኙ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ በየመን መንግስት እገታ ሲፈጸም ድርጊቱን ለመቃወም የማስቀድመው ጥያቄ "አቶ አንዳርጋቸው የታገሉለት፣ ዋጋ የከፈሉለት እና አሁንም ለእስር የበቁለት አላማ ምንድነው?" የሚለው ነው፡፡ ይህ አላማ የሁላችንም ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን አላማ ነው፡፡ ስለዚህ የምንመርጠው የትግል ስልት የትኛውም ቢሆን የአንዳርገቸውን እስር በተመለከተ ግን አቋማችን አንድ ነው፡፡
የነDaniel Berhaneን አመክኒዮ እንከተል ካልን ግንቦት ሰባትም የሰላማዊ ታጋዮችን የነአንዷለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ናትናኤል መኮንን ወዘተ በግፍ መታሰር በማውገዝ ከጎናችን መቆም አልነበረበትም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይህን አላደረገም፡፡ ይልቁንስ ትልቁን ስዕል - ማለትም አንዷለም የታሰረለትን፣ ከቤተሰቡ የመለየት ዋጋ የከፈለለትን የነጻነት መሻት አላማ ከተከተለው ሰላማዊ የትግል ስልት ነጥሎ በማየት እስሩን አውግዟል፡፡
አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ሰፍኖ ለማየት ላላቸው አላማ ስልጣናቸውን ከፍለዋል - ሐብታቸውን ከፍለዋል (በስርዓቱ የተወረሰባቸውን ግዙፍ ህንጻ ያስታውሷል) - ለቤተሰባቸው የሚሰጡትን ጊዜ ከፍለዋል - የዘመዶቻቸውን ደህንነት ከፍለዋል (በአባታቸው ላይ የተፈፀመውን እስር ያስታውሷል) - በአጠቃላይ የግል ህይወታቸውን ከፍለዋል፡፡ አሁንም የበለጠ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል አደጋ ላይ ወድቀዋል፡፡ እያንዳንዳችን ስለ አላማችን ስንል የከፈልነውን ዋጋ ከርሳቸው ጋር ስናነጻጽር በልባችን ውስጥ ላቅ ያለ ክብር ልንሰጣቸው ግድ ይለናል፡፡
ማወቅ ያለብን ዋናው ነገር ስርዓቱ በዚህ ወይም በዚያ መንገድ ካከተመ በኋላ በሁለቱም ጎራ ባሉ ድርጅቶች መካከል ያለው የስልት ልዩነት እንደሚያበቃለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ልዩነት ካለ የሰለጠነ የአይዲዮሎጂ ልዩነት ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሲጠቃለል - "ተነጣጥላችሁ ተቃወሙኝ" ለሚለው የተለመደው የአምባገነኖች ጥያቄ ምላሻችን በዘመኑ ቋንቋ "መስሚያችን ጥጥ ነው" የሚል ነው፡፡

No comments:

Post a Comment