ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ:- ”…ይህን የውሃ ንብረቷን በቁጥር እየጨመረ ለሚሄደው ሕዝቧና በማደግ ላይ ላለው ኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል ማድረግ የኢትዮጵያ ተቀዳሚና የተቀደሰ ግዴታዋ ነው።…”
አባይን ለመንከባከብ የጎሰኛነት አገዛዝ በዲሞክራሳዊ አገዛዝ መተካት አለበት
ክፍል አንድ
“ለምንወደው ለዛሬው ሕዝባችንም ሆነ፤ ከዘመን ወደ ዘመን ለሚከተለው ትውልድም ጭምር፤ የዓባይን የውሃ ሃብት ለሕይወቱ ደህንነትና ለፍላጎቱ ማርኪያ እንዲውል ማድረግ፤ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጠውና በቅድሚያ የሚያሳስባት ጉዳይ ነው።አምላካችን ያበረከተላትን ይህን ሃብቷን ለሕዝባቸው ህይወትና ደህንነት በማዋል እንዲጠቀሙበት ከጎረቤት ወዳጅ አገሮች ጋር በለጋስነት በጋራ ለመካፈል ዝግጁ ብንሆንም፤ ይህን የውሃ ንብረቷን በቁጥር እየጨመረ ለሚሄደው ሕዝቧና በማደግ ላይ ላለው ኢኮኖሚ ጥቅም እንዲውል ማድረግ የኢትዮጵያ ተቀዳሚና የተቀደሰ ግዴታዋ ነው።”ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ጥቅምት 1957 ዓም
“ወንዞችን በጋራ ፈሰስ የሚጋሩ አገሮች ሁሉ ውሃውን አግባብ፤ ፍትሃዊ፤
ለሁሉም ጠቃሚ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብትና ግዴታ አለባቸው። ይህን ሲያደርጉ በተቻለ መጠን ለጋራ ጥቅም
በመመካከርና አንዱ ሌላውን ሳይጎዳ፤ ውሃውንና አካባቢውን ዘላቂነት ባለው መንገድ በመንከባከብ ይሆናል።”
Convention on the Law of the
Non-navigational Uses of International Watercourses, UN General Assembly
resolution 43/52 of December 1994.
አባይን የመጠቀም ጥያቄ አጼ ኃይለ ሥላሴ ከላይ ከተናገሩት በበለጠ ደረጃ
ዛሬ ወሳኝ ሆኗል። ባሁኑ ወቅት በዓለም አከራካሪ፤ አሳሳቢና ጦርነትን ፈጣሪ ከሆኑ አንኳር ጉዳዮች አንዱ ውሃንና
ወንዞችን የመጠቀም መብት ነው። ከፍተኛ ሽሚያና ሴራ አለ። ጉዳዩን ያጠኑ ግለሰቦችና ተቋሞች እንዲህ ይላሉ። “የዛሬ
አስራ ስድስት ዓመት (2030) የዓለም ሕዝብ ብዛት እየጨመረ፤ ፍላጎት እያደገ፤ ከተሜነትና ልማት እየተስፋፋ
ስለሚሄድ፤ አራት ቢሊዮን ሕዝብ የውሓ እጥረት ያጋጥመዋል። ከዚህ ውስጥ ብዙ መቶ ሚሊዮን የሚገመተው በአፍሪካ
ቀንድ፤ በሰሜን አፍሪካ፤ በሳሄል አገሮች ይገኛል።” ከሳሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሕዝብ ዛሬ አንድ ነጥብ
አንድ ቢሊዮን ሲገመት፤ በተባበሩት መንግሥታት ስሌት፤ በ2050 ይህ ቁጥር ወደ ሁለት ነጥብ አራት ቢሊዮን ከፍ
ይላል። የውሃ ተፋሰስ ተፎካካሪ ወደ ሆኑት ግብጽና ኢትዮጵያ ብናተኩር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ዛሬ ካለው እጥፍ
ይሆንና ቢያንስ መቶ ሰማንያ አምስት ሚሊዮን ይደርሳል። ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ከገመተው ዝቅ ብሏል ማለት
ነው። በአንፃሩ፤ የግብፅ ሕዝብ ብዛት መቶ ሃያ አምስት ሚሊዮን ይሆናል። ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት ግብፅን በስድሳ
ሚሊዮን ሕዝብ ትበልጣለች ማለት ነው። ሆኖም፤ ከግብፅ ጋር ለመወዳደር፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ አንድነት፤ የመላዊ
ሕዝቧን ኢትዮጵያውይነት መቀበል ወሳኝ ነው። በተጨማሪ ሁሉም ኢትዮጵውያን የሚሳተፉበትና ክፍጹም ድህነት
የሚላቀቁበትን ዘላቂና ፍትሃዊ ኢኮኖሚ መመስረት ያስፈልጋ። ማንኛውም አገር በአፈና፤ በጎሰኛንትና በስደት በተበከለ
አገዛዝ ጠንካራ ሕብረተሰብና ጥንካራ አገር ለመመስረት አይችልም። ኢትዮጵያ ታሪክ ያላት፤ መነሻና መድረሻ ያላት፤
ታላቅ ለመሆን የምትችል፤ የብዙ ብሄር/ብሄረሰብ ደሴት መሆኗን ተቀብለን ከልዩነቶች በላይ የሚገልጻት ዋናው እሴት
ኢትዮጵያ አንድ አገር መሆኗን መቀበል፤ ዜግነት ኢትዮጵያዊ እንጅ ጎሳዊ አለመሆኑን በማንኛውም ግንኙነት ማስተጋባት
የወቅቱ ጥያቄዎች ናቸው እላለሁ። ይኼን የተቀደሰ መርህ እንደዋዛ ካየነው፤ ኢትዮጵያን ለሌሎች (ጥቂት ተጠቃሚዎችና
ለፈረንጆች) እንደምናስተላልፋት በአይናችን እያየን ነው። ዛሬ ኢትዮጵያውያን በጎሳ ስለተከፋፈሉ፤ መብታቸውና
ነጻነታቸው ስለታፈነ በሃገራቸው የተፈጥሮ ሃብት፤ በቤታቸው፤ በመሬታቸው፤ ብህይዎታቸ፤ በሃብታቸው፤ ለማዘዝ
አይችሉም። ለመጀመሪያ ጊዜ ፈረንጆች ከኢትዮጵያዊን የበለጠ ተሰሚነትና መብት አላቸው። አስደናቂውና የሚያኮራው
የመሰረታዊ ለውጥ ምልክት ወጣቱ ትውልድ “መብት ይጠየቃል፤ አይለመንም፤ ፍርሃት አልወለደንም፤ በህሊናየ አታዝም”
እያለ በደሴ፤ በሃህር ዳር፤ በጎንደር፤ በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች የሚያሰማው ድምፅ ነው። ሌሎቻችን እጆቻችን
አጣጥፈን የምንመለከት ጊዜ ያለፈ ይመስለኛል። [ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]
No comments:
Post a Comment