Tuesday, June 17, 2014

በምኒልክ ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች ሲፈተሹ በዘመናችን ያሉ ብሄርተኛ ጸሃፊዎች ባገኙት መድረክ ላይ ሁሉ በምኒሊክ ላይ ቀፋፊ ስድቦችን እና ውንጀላዎችን ይሰነዝራሉ፡፡ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ምኒልክ እንከን አልባ መሪ ነው የሚል እምነት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ የአድዋውን ባለድል ታላቅ መሪነት ተጠራጥሮ አያውቅም ፡፡

አዎ እኔም የእብድ የቃውስ የሸርሙጣ ትርጉም ለነፃነት የሚታገሉ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብክ ግፈኞችን የሚታገል…ለኢትዮጵያዊነት የሚኖር ከሆነ አዎ እብድ ነኝ አዎ ቀውስ ነኝ አዎ ሸርሙጣ ነኝ እላቸዋለው፡፡
በምኒልክ ላይ የሚቀርቡ ውንጀላዎች ሲፈተሹ
በዘመናችን ያሉ ብሄርተኛ ጸሃፊዎች ባገኙት መድረክ ላይ ሁሉ በምኒሊክ ላይ ቀፋፊ ስድቦችን እና ውንጀላዎችን ይሰነዝራሉ፡፡ የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ምኒልክ እንከን አልባ መሪ ነው የሚል እምነት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ የአድዋውን ባለድል ታላቅ መሪነት ተጠራጥሮ አያውቅም ፡፡ የዳግማዊ ምንሊክ አስተዳደራዊ ስኬቶች እና ጉድቶች ሚዛናዊ በሆነ ሂስ መፈተሽ ጤናማ ነው ብሎ ያምናል፡፡
የጊዜው ፋሽን ከዚህ ለየት ይላል፡፡ ምኒልክን ማሄስ ሳይሆን ምናባዊ ወንጀሎች እየፈጠሩ ጭራቅ አድርጎ መሳል ተለምዷል፡፡ በንጉሰ ነገስቱ ላይ የሚቀርቡት የፈጠራ ወንጀሎች ለብዙ ጊዜ በመደጋገማቸው የተነሳ፣ የተረጋገጡና ያለቀላቸው እውነቶች ሆነው ተወስደዋል፡፡ ረጋ ብለን ስንፈትሻቸው ግን ፣ ውንጀላዎቹ በጥላቻ ከተሞላ ልብ የተፈለፈሉ ተረቶች ሆነው እናገኛቸዋልን፡፡ ለዛሬ ምኒልክ የብሄረሰቦቹን ስም በማጉደፍ እና የተፈጥሮ ሀብት በማጥፋት የቀረቡባቸውን ውንጀላዎች እንፈትሻለን፡፡
ምኒልክ ለብሄረሰቦች የስድብ ስም አውጥቷልን
አቶ አብርሃም በንቶ የተባሉ ጸሃፊ ‹‹ለምለሚቱ ወላይታ›› በተባለው መጽሃፋቸው የሚከተለውን ጽፈዋል፡ ‹‹ምኒልክ በወላይታ ድልን ከተጎናጸፈ በኋላ ህዝቡን በመናቅ ወላሞ ብለው ያለ ስሙ ስም አወጡለት››(ገጽ 40)
ተስፋዬ ገ/አብም የ‹‹ቡርቃ ዝመታ›› በተባለው ልብ ወለዱ ላይ ሀወኒ የተባለችውን ዋና ገጸ ባህሪ እንዲህ ያናግራታል፡-
‹‹… አንዳንዶች የወላይታን ህዝብ ታሪክ ባለማወቅ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወላሞ እያልን ስንጠራቸው ነበር፡፡ የወላይታ ህዝብ ወላሞ የሚለውን ስያሜ አለመቀበል ብቻ ሳይሆን ቃሉን ሲሰማ ክፉኛ ይቆጣል፡፡ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ወላሞ የሚለው ቃል ዋ ላሞ ከሚለው የመጣ ነው፡፡ ነፍጠኞች ከብቶች ናችሁ፣ ላሞች ናችሁ፣ ሊሏቸው ሲፈልጉ እንደዘበት የብሄረሰቡ አባላት ላይ የለጠፉት የንቀት ስያሜ ነው፡፡ ምኒልክና ነፍጠኞቹ የፈለሰፉትን ይህን ስድብ የሃይለስላሤ መንግስት እንዳለ ተቀብሎ ነበር ያስተናገደው፡፡›› (ገጽ 285)
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ሁለት ትልልቅ የተሳሳቱ መልእክቶች ይገኛሉ፡፡
1ኛ. ወላሞ የሚለውን ቃል የፈለሰፉት ምኒልክና ነፍጠኞቹ ናቸው፡፡
2ኛ. ወላሞ የሚለው ቃል ዋ ላሞ ከሚለው አማርኛ የመጣ ነው፡፡
እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ወላሞ የሚለው ቃል ምኒልክ ከመወለዳቸው በፊት ብዙ ዘመናት አስቀድሞ ይታወቅ ነበር፡፡ ሌለው ቢቀር በ1559 እንደ ተጻፈ በተረጋገጠው ፉትህ አል ሃበሻ በተባለው የየመኑ ታሪክ ጸሀፊ ድርሳን ውስጥ በግልጽ ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡ (the conquest of Abyssinaia Trans. By Lester Sten house መጽሃፍ ውስጥ ገጽ 332 ላይ ይመልከቱ) እንዲሁም የምኒልክን አያት ሳህለስላሴን የጎበኘው ክራፍ በመጽሃፉ ውስጥ ቃሉን መዝግቦታል፡፡ ስለዚህ ምኒልክና ነፍጠኞቹ ወላሞ የሚለውን ቃል ፈለሰፉት የሚባለው ተራ ስም ማጥፋት ነው፡፡
ወላሞ የሚለው ቃል የወላይታን ህዝብ ላሞች ናችሁ ለማለት የተፈጠረ ነው የሚለው ሃላፊነት የጎደለው ቀልድ ነው፡፡ ለዚህ አፍራሽ ውንጀላ የስነ-ልሳንም የታሪክ ማስረጃ አይገኝለትም፡፡
ወላሞ የሚለው ቃል መናሻው ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ቃሉ ስድብ መሆኑን የሚገልጽ አሳማኝ ማስረጃ ግን የለም፡፡ በዘመነ መሳፍንት የዛሬውን ደቡብ ኢትዮጵያ የጎበኘው እንግሊዛዊው ሊቅ ቤኪ፣ ወላሞ የሚለው ቃል የኦሮሞዎች አጠራር ዘይቤ መሆኑን፣ ‹‹ወላይታን አስመልክቶ ወላሞ የሚለው መጠሪያ የኦሮምኛ ውክልና ያለው ነው፡፡›› ሲል ጽፏል፡፡
(Respecting wolita … this is the native name, Wolamo being the Oromo designation)
ተስፋዬ ገ/አብ በተጠቀሰው መጽሃፉ ስለ ጃንጀሮ የሚለንን እንስማ፡፡
‹‹ደርግም ጃንጀሮ የሚለውን ስያሜ ተቀብሎ አሁን ድረስ ይጠቀምበታል፡፡ ጃንጀሮ በሚል ስያሜ የሚጠራው ብሄረሰብ ትክክለኛ ስም የም ነው፡፡ ጃንጀሮ የተባሉት ተራራ ላይ ወጥተው ወራሪያቸውን በድንጋይ ሰለፈጁት ነው፡፡ ዝንጀሮ ለማለት ዝንጀሮ የሚል ስያሜ ሰጥተው ህዝብን የሚያህል ነገር በደንታቢስነት የሚያዋርዱት፡፡ የነፍጠኛው ስርአት ክርፋት እዚህ ድረስ ጠልቆ ሊሰማን ይገባል፡፡››
ተስፋዬ ጃንጀሮ በሚል ሲጠራ የነበረው ህዝብ ትክክለኛ ስሙ የም ነው መሆኑን የገለጸው እውነት ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ የመጣው ድምዳሜ ግን አቦ ሰጡኝ ይመስላል፡፡ ጃንጀሮ የሚለው ስያሜ ምንጭ ምንድነው ምኒልክ ገና ነፍስ ሳያውቁ፣ ደቡብ ኢትዮጵያንና ኦሮሞን ያጠናው የፈረንሳዩ ሊቅ እንቶኒዮ የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ በተባለው ጥናቱ የሚከተለውን ይለናል፡፡ ‹‹የም የጃንጀሮ ህዝብ የሚጠራበት ስም ሲሆን ይሄ የመጨረሻው ስም ግን በካፋ ሰዎችና በኦሮሞዎች የተሰጣቸው ስያሜ ነው፡፡›› (ገጽ 71 ትረጉም የኔ)
(yamma est nom national de janjiro.ce deriner nom leur est donne par les gens de kaffa et par les Oromo)
ቤኪም ትንሽ ለወጥ አድርጎ ‹‹የሃገሩ አገረኛ መጥሪያ ያንጋሮ ሲሆን፣ ጃንጃሮ የሚለው ግን የኦሮሞ አጠራር ነው›› ይላል፡፡
(The native name of the country is yangaro as I have heard from the mouth of several natives, janjero being the Oromo pronunciation of the word)
በብሄርተኛ ምሁራን ዘንድ በአጤ ምኒልክ ላይ ከሚቀርቡ ክሶች አንዱ በወራራ የያዙትን የብሄረሰቦች የተፈጥሮ ሀብት በዝብዘዋል ወይም አውድመዋል የሚል ነው፡፡
ለምሳሌ ገዳ መልባ የተባለ ጸሀፊ ‹‹ኦሮሚያ›› በተባለ መጽሃፉ የሚከተለውን ውንጀላ ያዘንባል፡፡
‹‹ምኒልክ የኦሮሞን ተወላጅ በገፍ ባርነት ሸጠው ቁጥሩን እንዳላቀጨጩት ሁሉ፣ የኦሮሚያ ብርቅዬ የዱር አራዊቶችም አልተረፏቸውም ፡፡… ደግሞ የሚገርመው የተወሰነ የዝሆን ጥርስ ለማግበስበስ ሲሉ ምኒልክ ለዝሆን አዳኞች ድጋፍና ፈቃድ መስጠታቸው ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ፖሊሲ ፍጻሜያቸውም አናብስትን እና ዝሆኖችን ከምድረ ኦሮሞ ማጥፋትን አስከተለ፡፡›› ለዱር አራዊት አራዊት መጥፋት ተጠያቂ የምኒልክ ፖሊሲ ለውን ምኒልክ እና ሰራዊቱ የኦሮሞን ምድር ከመርገጣቸው በፊት በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደሚደረገው የኦሮሞ ጎረምሶች ዝሆን እና አንበሳ ማደን አንዱ የኑሮ ዘይቤያቸው ነበር፡፡ ዲ ሳልቪያክ የተባለው አፍቃሬ ኦሮሞ ጸሀፊ እንደ ዘገበው፣ በኦሮሞ ባህል አደን የክብር ምንጭ ነበር፡፡ አንበሳ መግደል ‹kan lencca› ፣ ዝሆን መግደል ‹kan arba›፣ አውራሪስ መግደል ‹kan wersesa›፣ ግስላ መግደል ‹kan qerransa› ተብሎ ይታወቃል ብሎ ዘግቧል፡፡
ይሄው ጸሀፊ ኦሮሞ አዳኞች ዝሆን የሚያድኑበትን መንገድም ሲነግረን ‹‹ኦሮሞዎች የነጮችን መሳሪያ(ጠመንጃ) ከመጠቀም ይልቅ በራሳቸው መንገድ ዝሆን ያድናሉ፡፡ ተነጣጥለው የሚቆሙትን ዝሆኖች በፈረስ እያባረሩ ይገድላሉ›› ይላል፡፡
በዚህ አይነት ለክብር ሲባል ብቻ በኦሮሞ ምድር ስፍር ቁጥር የሌለው ዝሆን ተጨፍጭፏል፡፡
በአማርኛ ቋንቋ የዝሆን አደንን የሚገልጹ ቃላት በብዛት የአፋን ኦሮሞ ተጽዕኖ ያረፈባቸው ለመሆናቸው የሚከተለው መህተመስላሴ ወልደመስቀል አንቀጽ ማሰረጃ ይሆነናል፡፡ ደራሲው በቀድሞ ዘመን አደን በማህበራዊ ህይወት ውስጥያለውን ፋይዳ ሲተነትኑልን እንዲህ ይላሉ ፤
‹‹አዳኙ አስቀድሞ መራዉን የተወጣ ሰው የገደለ የሆነ እንደሆነ ስለአርባ ሰው አለዚያ እንደ አንድ ሰው ግዳይ ብቻ ይቆጠርለታል፡፡ ሲገድልም አዶና ቁቤላ የሚባለውን የዝሆን እግር ሰንጥቆ ያመጣና ለሚስቱ እግሯ እና እጇ ላይ ያስርላታል፡፡ ራሱ ባንድ ጆሮው የወርቅ ሎቲ ያደርጋል፡፡ ስድሰት ዝሆን ሲገድል ኤልካ ሰበረ ይባላል፡፡ በዚህ ጊዜ የዝሆን ጉትቻ ያደርጋል፡፡›› (ዝክረ ነገር፣ ገጽ 342)
በዚህ አንቀጽ ውስጥ ያሰመርኩባቸው ቃላት በሙሉ የአፋን ኦሮሞ ቃላት ናቸው፡፡
- ቁቤላ (qubeelaa) ቀለበት፣
- ሎቲ (looti) ዝሆን ገዳይ ጆሮው ላይ የሚሰካው ምልክት፣
- ኢልካ(ilka) የዝሆን ጥርስ እና
- ጉትቻ (gutichaa) የዝሆን ገዳይ ሚስት የምታደርገው የጆሮ ጌጥ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
ቸሩሊ የተባሉት ጣሊያናዊ ሊቅ ከሰበሰቧቸው የኦሮሞ ህዝብ ዘፈኖች መካከል ብዙዎቹ ዝሆን ገዳይን የሚያወድሱ እንጂ ስለ አራዊት ጥበቃ የሚሰብኩ አልነበሩም፡፡
ይህንን ስንመለከት፣ ለብርቅዬ አራዊት ውድመት አስተዋጽኦ ያደረገው ህዝቦች ባህል የመተቸት ወኔ አጥተው፣ ለሀገር ኢኮኖሚ(ጥርሱን ለመሸጥ) ሲባል ዝሆን በአግባቡና በስርአት የሚያሳድዱትን ምኒልክን የሚያወግዙ ምሁራን፣ ብሄርተኝነት ምን ያህል የህሊና ሚዛን እንደሚያቃዉስ ማሳያ ነቸው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ዳግማዊ ምኒልክ ከህዝብ ባህል ጋር እየታገሉ፣ ስርአት የለሽ አደን እንዲቀር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ማስታወስ አለብን፡፡ ለአብነት ያክል፤ ጥቅምት 1901 አ.ም ባወጡት አዋጅ የሚከተለው ቃል ሰፍሯል፤ ‹‹ሳያስፈቅድ ያደን ወረቀት በዞረበት ሳይቀበል፣ አውሬ ሲያደን የተገኘ ሰው አምስት አመት ይታሰራል፡፡ ጠመንጃውም ጥይቱም ውርስ ሆኖ ወደ መንግስት ይገባል፡፡›› የዚሁ ህግ አንቀጽ 4 የሚከተለውን ብርቱ ሃይለቃል ይዟል፤ ‹‹ከወሰንም አልፎ አውሬ ለማዳን ወይም ለሌላ ጉዳይ፣ ሌላ አገር ግዛት ሄዶ የተገኘ ሰው፣ ቅጣቱ ያስር አመት እስራት ነው፡፡›› (ዝክረ ነገር ገጽ 349)
ከነዚህ ማስረጃዎች አንጻር ስንመዝነው ከላይ የተጠቀሰው የአቶ ገዳ መልባ ውንጀላ መሰረተቢስ ክስ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡
በወርቁ ፈረደ
ይቀጥላል

No comments:

Post a Comment