Tuesday, June 17, 2014

አህያውን ትቶ ዳውላውን(በትግሬዎች ወገኖቻችን ላይ ያለው የተሣሣተ ዘመቻ)

አዎ እኔም የእብድ የቃውስ የሸርሙጣ ትርጉም ለነፃነት የሚታገሉ ኢትዮጵያዊነትን የሚሰብክ ግፈኞችን የሚታገል…ለኢትዮጵያዊነት የሚኖር ከሆነ አዎ እብድ ነኝ አዎ ቀውስ ነኝ አዎ ሸርሙጣ ነኝ እላቸዋለው፡፡
አህያውን ትቶ ዳውላውን
June 17/2014
(በትግሬዎች ወገኖቻችን ላይ ያለው የተሣሣተ ዘመቻ)
በአሁኑ ሰዓት በአብዛኛዎቹ ኢትዮጵያዊ የዜና መለዋወጫ መስኮች፤ “ትግሬዎች በዚህ መንግሥት ተጠቅመዋል? ወይንስ አልተጠቀሙም?” የሚለው ጉዳይ ዓይነታ መወያያ ሆኖ፤ መድረኮቹን ሁሉ አጣቦ ይዟል። በመጀመሪያ ደረጃ፤ አንድን ጉዳይ ኢትዮጵያዊ ታጋዮች ሲያነሱ፤ ከትግሉ ዋና ግብ አንጻር ነው። እንዲያው ለወግ ያህል ወይንም ቁጭትን ለመዘርገፍ የሚደረግ ውይይት፤ የታጋዮችን ቀልብ አይስብም። ይኼ ጉዳይ በትግሉ ሂደት ውስጥ ለኢትዮጵያዊ ታጋዮች ምን ይጠቅማል? ትግሉን ወደፊት ከመግፋትና ከግቡ ከማድረስ አኳያ ምን አስተዋፅዖ አለው? ይኼ ወሳኝ ነው።
ትግል በመርኅ የሚካሄድ እንጂ፤ በየተመቸው የሚነዳ መንፈስ አይደለም። በትግሬዎችና ራሱን “የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ በተነሳው ድርጅት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። በእርግጥ የዚህ ግንባር አባላት በሙሉ ትግሬዎች ናቸው። ይኼ በግልፅ ያለና የማያጠያይቅ ነው። ደጋፊዎቹም በአብዛኛው ከዚሁ ወገን መሆናቸው አያስገርምም። ነገር ግን በአማራው ላይ አማራ ነህ ተብሎ መጠቃቱን እያወገዝኩ፤ አኝዋኩ በአኝዋክነቱ መጠቃቱን እያወገዝኩ፤ ትግሬው በትግሬነቱ እንዲጠቃ ሲዘጋጅ ዝም ብዬ የማይበት ዓይን የለኝም። ትግሬውን እንደ አማራው፣ እንደ ኦሮሞው፣ እንደ አኙዋኩ፣ እንደ ሲዳማው፣ እንደ ኦጋዴኑ ልቆምለት ካልቻልኩ፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለቴ ውሸታም ያሰኘኛል።
ይህን የማራምደው ትግሬዎችን ወደ ትግሉ ሠፈር ለማምጣት ካለኝ ምኞት አይደለም። አንድ ትግሬም ሆነ አማራ፤ ኦሮሞም ሆነ አኙዋክ፤ ወደ ትግሉ የሚመጣው፤ የትግሉን መርኅ ስላመነበት እንጂ፤ የግል ጥቅም አገኛለሁ ብሎ አይደለም። እንዲህ ያለው፤ ካለበት ቢቆይ ጥቅሙ የበለጠ ይጠበቅለታል። እኔ ይኼን የማራምደው፤ በትግሬዎች ወገን የሚጠቃ የትግሬ ዘመድ ስላለኝ አይደለም። ይኼን የማራምደው የግል ጥቅም የማገኝበት መንገድ ስላለኝ አይደለም። ይኼን የማራምደው ስለማምንበትና ትክክለኛ መርኄ ሰለሆነ ነው፤ ኢትዮጵያዊነቴ ስለሚያስገድደኝ ነው፤ ታጋይነቴ ስለሚያስገድደኝ ነው።
መረዳት ያለብን፤ ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት ለሥልጣን መያዣና አሁንም የሥልጣኑ ማራዘሚያ አድርጎ የያዘው፤ አማራውን በአማራነቱ በማጥቃት ነው። ለአማራው ማጥቂይ አድርጎ ያቀረበው ደግሞ፤ አማራው ተጠቃሚ ነበር፣ አማራው የሥልጣን ባለቤት ነበር፣ አማራው ገዝቶናል፣ በማለት ነው። ይህ ደግሞ መሠረታዊ የሆነውን ኢትዮጵያዊያን ከ፲ ፱ ፻ ፷ዎቹ ተማሪዎች ጀምረው የተነሱለትን በጨቋኝና በተጨቋኝ፤ በገዥዎችና በተገዥዎች መካከል የነበረውን እንቅስቃሴ በመጥለፍ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአማራው ወገን ሌሎችን በመግዛቱ ነው የሚል የፖለቲካ ስልት በማርቀቅ፤ አነስተኛው ክፍል ብዙኀንን የሚገዛበት ቀመር በማጠንጠን ነው።
እየገዛን ያለው ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት ነው። ትግሬዎች ተጠቃሚ ናቸው፣ ትግሬዎች ገዙን፤ የሚለው እምነት፤ ጠንከኛ ነው። የዚህን መንግሥት የፖለቲካ ተግባር ትክክል አይደለም የሚል የረጋ አእምሮ ያለው ሰው፤ ዛሬ በተገላቢጦሽ፤ ትግሬዎችን በአማራዎች ተክቶ በትግሬዎች ላይ ዘመቻ ማድረግ፤ አንድም የዚህን ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ እንዲቀጥል ማራገብ ነው፤ ከዚህ ወዲያ ደግሞ እንደዚሁ ወገንተኛ ወራሪ ግንባር የራስን ወገን ለማሰባሰብ የተወረወረ ዘዴ ነው። በሁለቱም በኩል አፍራሽና የኢትዮጵያዊነት ጠር ነው። ይህ ማለት ለዚሁ መንግሥት ያደሩ አልተጠቀሙም ማለት አይደለም። ሆዳቸውን ያመለኩ ግለሰቦች፤ ለዚህ መንግሥት ስግደው ያደሩ ተጠቅመዋል። ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች አቧራቸውን ተሸካሚም ሆነውም ለዚህ የትራፊ ለቃሚዎች አሉ። እኒህም ተጠቃሚዎች ናቸው። ከነዚህ ሆድ አደሮች የትግሬነት ደም ጠብታ በሰውነታቸው ቢፈለግ አይገኝም።
ስለዚህ፤ የስርዓቱ ደጋፊና ስርዓቱን የሚቃወሙ በሚል ብቻ ነው፤ ኢትዮጵያዊያንን ታጋዮች ኅብረተሰቡን የሚከፋፍሉ፤ ድሮም ሆነ ዛሬ። እዚህ ላይ ተጋዮች የሚለውን አሰምርበታለሁ።
የፖለቲካ አመለካከትንና ተግባርን በዘር ላይ የተመሠረ አድርጎ መመልከት ዘረኝነት ነው። በገዥው ክፍልም ሆነ በታጋዩ ክፍል፤ የፖለቲካ አመለካከትን ከግለሰብ አውጥቶ ከአንድ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ማቆራኘት ስህተት ነው። ይህ አጥር የሌለበት ጉዳይ ነው። ለዚህኛው ይሠራል ለዚያኛው አይሠራም ልንል አንችልም። የወደፊቷ ኢትዮጵያ የሁላችን ኢትዮጵያዊያን እንጂ፤ አንዱን ክፍል የሚጠቅም ወይንም የሚጎዳ መሆን የለበትም። ዛሬ በአማራዋ ላይ እየተፈጸመ ያለው ነገ በትግሬዋ ላይ እንዲደገም አንፈልግም። እናም መላ ኢትዮጵያዊያን፤ ትግሬዎችን ሆኑ ሌሎቹ በዚህ መንግሥት ላይ በአንድነት መነሳት አለብን። የፖለቲካ አመለካከታችን በግለሰብ እንጂ የትውልድ ሐረግ በመምዘዝ መሆን የለበትም።
የኢትዮጵያዊያን ጠላት ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት እንጂ፤ ተጠቀመም አልተጠቀመም፤ የትግራይ ወገናችን አይደለም። ኢትዮጵያ ስንል በወርድና ስፋቷ የሚኖረውን ህዝብ በሙሉ እንጂ፤ አንዱን ክልል ለይተን ነው አይደለም ልንል አንችልም። የፖለቲካ ቁማር መጫወት ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት ባህርይ እንጂ፤ የታጋዮች ባህርይ አይደለም። አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት ዛሬ ትግሬዎችን ራሱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው መንግሥት ሙሉ ደጋፊ ናቸው ወይንም በዚህ መንግሥት ምክንያት ተጠቃሚ ናቸው ብሎ እንደ አጀንዳ ማራገብ፤ የዚሁ መንግሥት መጠቀሚያ ከመሆን አያልፍም። ከዚያ ካለፈ ደግሞ፤ የራስን ወገን ለይቶ ነፃ አውጪ ግንባር ለማቋቋም መንገድ የማዘጋጃ ሩጫ ነው። ይህ መንግሥት ሊወድቅ የሚችለው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተነስተን፤ ኢትዮጵያዊያን ነን ብለን ስንቆም ነው። ከዚህ የተለዬ መንገድ፤ የዚህ መንግሥት መጠቀሚያ መሆን ነው።
አንዱ ዓለም ተፈራ፤ የእስከመቼ አዘጋጅ፤

No comments:

Post a Comment